| አገራችን አለም ወደሚጓዝበት የዲጂታል ብሮድካስት ቴክኖሎጂ በፍጥነት ለመግባት ትችል ዘንድ ሰፊ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሚኒኬሽን ሥራዎች ከወዲሁ መሠራት እንዳለባቸው ተገለፀ፡፡
ይህ የተገለፀው ትናንት የባለሥልጣኑ የሰው ሀብት አመራርና ልማት የሥራ ሂደት እና የሩዋንዳ ትምህርታዊ ጉብኝት ተሳታፊ ባለሙያዎች ለባለሥልጣኑ ሠራተኞች በዲጂታል ብሮድካስት እና ተሞክሮ ልውውጥ ዙሪያ ባዘጋጀው የግማሽ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ላይ ነው፡፡
የባለሥልጣኑ ባለሙያዎች አቶ አያሌው ጌታነህ፣ አቶ ግዛው ተስፋዬ እና አቶ ሽፈራው ሰለሞን የዲጂታልብሮድካስትምንነትና ጥቅም፣ ትኩረትየሚሰጣቸውጉዳዮችእናየሩዋንዳየዲጅታላይዜሽንተሞክሮ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በቅደም ተከተል ፅሁፎችን አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በአናሎግና ዲጂታል ብሮድካስት መካከል ብዙ የቴክኖሎጂና የጠቀሜታ ልዩነት በመኖሩ ዓለምአቀፉን የቴሌኮሙኒኬሽን ዩኒየን /ITU/ እ.ኤ.አ. በ2015 አገሮች ሁሉ ወደ ዲጂታል ብሮድካስት እንዲሸጋገሩ ያስቀመጠውን ገደብ ተግባራዊ ለማድረግ በርትተን እንሰራለን ተብሏል፡፡ ሆኖም ሽግግሩ የተሳካና የተሳለጠ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻዎች በተለይም የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ከፍተኛ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ሊሰሩ ይገባል ተብሏል፡፡ ለዚህም እንዲረዳ አስፈላጊ የሆኑ ግብረኃይሎችና ኮሚቴዎች መቋቋም እንዳለባቸውና ፍኖተ አቅጣጫም (Road Map) መዘጋጀት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡
የሽግግሩ ዓይነት፣ ፈተናዎች፣ ጊዜ፣ ደረጃና ምዕራፍ ከፖሊሲና ሕግ ማዕቀፍና አንፃር ቅደም ተከተሉን በጠበቀ መልኩ በጥንቃቄና በጥናት መፈፀም እንዳለበት በአጽንኦት ተገልጿል፡፡
ለሽግግሩ የሚያግዝ መረጃ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል አለን ወይ? ሽግግሩስ አልዘገየም ወይ? ለመሸጋገር የሚያስችለን የገንዘብና የማቴሪያል አቅም አለን ወይ? የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ሥራ በስፋት ለመስራትስ ምን ታስቧል? ሚዲያዎችስ ማኀበራዊ ኃላፊነትና ግዴታቸውን በሚገባ እንዲወጡ የሚሰራው የድጋፍና ክትትል ሥራ በቂ ነው ወይ? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች ከቤቱ ተነስተው በቂ ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሁሉም ሰው ውድ የሆነውን HD (High Definition) ቴሌቪዥን ገዝቶ መጠቀም ስለማይችል ሕብረተሰቡ አሁን እየተጠቀመበት ባለው አናሎግ ቴሌቪዥን መጠቀም እንዲያስችለው የዲጂታል ሥርጭትን ወደ አናሎግ ሥርጭት መቀየር የሚያስችል ሴት ቶፕ ቦክስ (Set Top Box) የሚያገኝበት ሁኔታ ከወዲሁ ሊታሰብበት የሚገባ በመሆኑ መሰል ጉዳዮችን ሁሉ ታሳቢ የሚያደርግ ፖሊሲ መር ስትራቴጂ መከተልን ይመረጣል ተብሏል፡፡ በመሆኑም በተቻለ መጠን ርካሽና በጣም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም እንዲቻል ባለስልጣኑ የራሱን መነሻ ፅሁፍ (Concept Paper) አጥንቶ ለበላይ አካል ያቀረበ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የብሮድካስት አገልግሎትን ከምድር ወደ አየር ወይም በሳተላይት ወይም በኬብል በማሰራጨት መስጠት እንደሚቻል ታውቋል፡፡ |