ጥያቄ 1. የመንግሥት (የሕዝብ) ብሮድካስት አገልግሎት ማለት ምን ማለት ነው?
መልስ:- ሕዝብን ለማስተማር፣ ለማሳወቅና ለማዝናናት በአገር አቀፍ ወይም በክልል የሚቋቋም ተጠሪነቱም ለፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ወይም ለክልል ምክር ቤቶች የሆነ በሙሉ ወይም በከፊል የመንግሥት በጀት የተመደበለት የሬዲዮ ወይም የቴሌቭዥን አገልግሎት ማለት ነው።
ጥያቄ 2. የንግድ ብሮድካስት አገልግሎት ማለት ምን ማለት ነው?
መልስ:- ትርፍን መሰረት ያደረገ፣ ሕዝብን ለማስተማር፣ ለማሳወቅና ለማዝናናት ሕጋዊ ሰውነት ባለው አካል የተቋቋመ የሬዲዮ ወይም የቴሌቭዥን አገልግሎት ማለት ነው።
ጥያቄ 3. ማኅበረሰብ ማለት ምን ማለት ነው?
መልስ:- አንድ የተለየ እና የተረጋገጠ የጋራ ፍላጎት ኖሯቸው በአንድ መልክአ ምድራዊ አካባቢ የሚኖሩ ወይም የጋራ ፍላጎት በሚያገናኛቸው የሕረተሰበ ክፍሎችን የያዘ ነው።
ጥያቄ 4. የማኅበረሰብ ሬዲዮ ማለት ምን ማለት ነው?
መልስ፡- በማሕበረሰቡ ፍላጎት ተቋቋመ፣ በማሕበረሰቡ የሚመራ እና የሚተዳደር ለትርፍ ያልተቋቋመ የሬዲዮ ብሮድካስት አገልግሎት ነው።
ጥያቄ 5.መልክአ ምድራዊ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ማለት ምን ማለት?
መልስ፡- መልክአ ምድራዊ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ማለትመልክአ ምድራዊ ክልልን ወይም ወሰንን መሠረት በማድረግ ከአሰፋፈር አኳያ በአንድ በተወሰነ አካባቢ ለሚኖሩ ማኅበረሰቦች አገልግሎት የሚሰጥ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ነው።
ጥያቄ 6. የጋራ ፍላጎት የማኅበረሰብ ሬዲዮ ማለት ምን ማለት ነው?
መልስ፡-“የጋራ ፍላጎት የማኅበረሰብ ሬዲዮ” ማለት ፆታን፣ እድሜን፣ ሙያን ወይም መሰል ሁኔታን መሰረት አድርገው ለተቋቋሙ የጋራ ወይም ተመሳሳይ ፍላጐት ላላቸው ማኅበረሰቦች አገልግሎት የሚሰጥ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ነው።
ጥያቄ 7. የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የማኅበረሰብ ሬዲዮ ማለት ምን ማለት ነው?
መልስ፡- “የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የማኅበረሰብ ሬዲዮ” ማለት በከፍተኛ የትምህርት ተቋም የመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ እገዛ የሚያደርግ እና ለተቋሙ ማኅበረሰብ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ነው።
ጥያቄ 8. ማኅበረሰብ ተኮር የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሬዲዮ ማለት ምን ማለት ነው?
መልስ፡- “ማኅበረሰብ ተኮር የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሬዲዮ” ማለት ለከፍተኛ ትምህርት ተቋም እና በተቋሙ አካባቢ ለሚገኙ ማኅበረሰቦች አገልግሎት የሚሰጥ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ነው።
ጥያቄ 9. ማኅበረሰብ ተኮር የአካባቢ አስተዳደር ሬዲዮ ማለትምን ማለት ነው?
መልስ፡- “ማኅበረሰብ ተኮር የአካባቢ አስተዳደር ሬዲዮ” ማለት በአካባቢው አስተዳደር እና ማኅበረሰብ የተቋቋመ እና ለአካባቢው ማኅበረሰብ አገልግሎት የሚሰጥ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ነው።
ጥያቄ 10. ቅሬታ ማለት ምን ማለት ነው?
መልስ፡- ቅሬታ ማለት በብሮድካስት አገልግሎት መብቴ ተነክቷል ወይም በአግባቡ አልተስተናገድኩም በማለት በብሮድካስተሮች ላይ የሚቀርብ አቤቱታ ነው፡፡
ጥያቄ 11. ጥቆማ ማለት ምን ማለት ነው?
መልስ፡- ጥቆማ ማለት በማናቸውም ብሮድካስተሮች ላይ የብሮድካስት አገልግሎትን አስመልክቶ ማስተካከያ ወይም እርምት እንዲደረግ ለባለስልጣኑ በሚቀርብ መረጃ የሚሰጥ አስተያየት ነው፡፡
|