የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ደስታ ተስፋው እና የኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ፅ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አዴሎ ጥር 10 ቀን 2004 ዓ/ም በአእምሮአዊ ንብረት ፅ/ቤት በጋራ ተባብሮ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
የመግባቢያ ሰነዱ ዓላማ የመገናኛ ብዙኃን በተለይም ከብሮድካስት አገልግሎት ተደራሽነት አንፃር በአዕምሮአዊ ንብረት ጥበቃ ሕጎችና አፈጻጸማቸውን አስመልክቶ ለህብረተሰቡ ተገቢ ግንዛቤና አመለካከት ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡ ህጎችን የጣሱ አሉታዊ ድርጊቶች ተፈፅመው ሲገኙም ከማጋለጥ እንፃር ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን በመገንዘብ ሁለቱ ባለድርሻ አካላት ተባብረው ለመስራት ነው፡፡
በፊርማ ስነስርዓቱም ላይ የተቋማቱ የስራ ኃላፊዎች በትብብር በመስራት የሚዲያውን አቅም ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገልፀው በትብብር መስራቱ የለውጥ ሰራዊት በመገንባት ሂደት ላይ የራሱ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት በመግባቢያ ሰነዱ መሰረት በጋራ መስራት እንዳለባቸው በመግለጽ አፈጻጸሙም በጋራ እየተገመገመ የአፈጻጸም አቅጣጫ በማስቀመጥ ለእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ስኬታማነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ |