A- A A+

አርስተ ዜና
  • Loading

ዜና

ሠራተኞች ለተሻለ ውጤታማነት መትጋት እንዳለባቸው ባለስልጣኑ ገለፀ

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የተጣለበትን ሀገራዊ ሃላፊነት ለመወጣት እንዲችል ሁሉም ሰራተኞች ፈጠራ የታከለበትን የአሰራር መንገድ በመከተል ውጤታማነት መጨመር እንዳለባቸው ገለፀ፡፡

የ2008 ዓ.ም.በጀት ዓመትን የስራ ዕቅድ በተመለከተ የሰራተኛውን ግንዛቤ ለማጎልበትና ለ2ኘው ዙር የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሳካት የሚያስፈልገውን ግብዓት ለማሰባሰብ የሚረዳ ውይይት ከሰራተኞች ጋር ተካሂዷል፡፡

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ልዑል ገብሩ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት ባለስልጣኑ ባለፈው በጀት ዓመት ብዙ አበረታች ስራዎች ያከናወነ ቢሆንም በተያዘው በጀት ዓመት ዲጂታላይዜሽንን ጨምሮ ብዙ አገራዊ ተግባራትን እንዲያከናውን ስለሚጠበቅበት ሰራተኞች ለተሻለ ውጤታማነት ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት የስራ ላይ ውጤታማነት የሚጎለብተው በጠንካራ የቡድን ስሜት በመንቀሳቀስ በመሆኑ ሰራተኞች ለቡድን ስራ ተግባራዊነት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ለአዶላ ሬዴ ወረዳ ማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ፈቃድ ሰጠ

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለሚገኘው ለአዶላ ሬዴ ወረዳ ማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ፈቃድ ሰጠ ፡፡ የፈቃድ አሰጣጥ ሥነ ስርዓቱ በአዶላ ሬዴ ከተማ አስተዳደር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ነሐሴ 05/2007 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡

የፈቃድ አሰጣጥ ሥነ ስርዓቱን በንግግር የከፈቱት የወረዳው ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ተወካይ፣ አቶ ዓለማየሁ ኃይሌ ሬዲዮ ጣቢያው የሚያስገኘውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ገልፀዋል ፡፡ አቶ ዓለማየሁ የጣቢያው መከፈት ዜጎች መረጃ የማግኘት እና ሃሳባቸውን በነፃነት የሚገልፁበት ሕገ-መንግስታዊ መብት በሀገራችን እውን መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡

ጣቢያው ለማኅበረሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት አጠናክሮ እንዲቀጥል የአከባቢው ሕዝብና የመንግስት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በፈቃድ አሰጣጥ ሥነ ስርዓቱ ከባለሥልጣኑ የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎች ለአከባቢው የመንግስት አመራሮች፣ ለጣቢያው ጠቅላላ ጉባዔና ቦርድ አባላት እንዲሁም ለአከባቢው ነዋሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ኢንዱስትሪ ከየት ወዴት?

በይታወቅ ባለምላይ-ከኢዜአ
መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት ካስቀመጣቸው አቅጣጫዎች አንዱ የኢትዮጵያን የመገናኛ ብዙሃን ኢንዱስትሪ ማሳደግ ነበር። እነሆ የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ተጠናቆ ሁለተኛው ሊጀመር ከወራት የማይበልጥ ጊዜ ቀርቶታል። ታዲያ በተጠናቀቀው የእቅድ ዘመን ኢንዱስትሪው የሚፈለገውን ያህል አድጓልን? የመገናኛ ብዙሃኑን እንዲደግፍና እንዲከታተል ኃላፊነት ከተሰጠው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ጋር ኢዜአ ቆይታ አድርጓል።
የባለሥልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ጣፋ ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ-ምልልስ እንዲህ ተዘጋጅቷል።
ኢዜአ፡- ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት የመጀመሪያውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አሰናድታ ወደ ስራ መግባቷ ይታወቃል። የአገሪቱን መገናኛ ብዙሃን እንዲደግፍና እንዲከታተል የተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በእቅድ ዘመኑ ለዘርፉ መጠናከር ምን ሰራ?
አቶ ወርቅነህ፡- የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን መገናኛ ብዙሃንን በተመለከተ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን አቅዶ አከናውኗል። በዋናነት መገናኛ ብዙሃንን የማስፋፋት ስራ ነው የሰራው። አጠቃላይ የብሮድካስትና የህትመት ሚዲያውን የማስፋፋት ስራ ሰርቷል።
የህትመትና ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃንን በማስፋፋት ረገድ ሰፊ ርቀት ተኪዷል። ብሮድካስትን በተመለከተ በመጀመሪያ ለመገናኛ ብዙሃን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው። የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፈቃዶችን ለመስጠት በቂ የሬዲዮ ሞገዶች መኖራቸውን ከማረጋገጥ አንፃር በእቅድ ዘመኑ 788 የሬዲዮና 483 የቴሌቪዥን ሞገዶች በዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት እንዲመዘገቡ ተደርጓል።
አገራችንም የህብረቱ አባል መሆኗና የሬዲዮ ሞገዶችን ማስመዝገቧ ለሚደረጉ የማስፋፊያ ስራዎች ትልቅ እገዛ ያደርግላታል። ከተመዘገበው ውስጥ ፈቃድ የተሰጠውን ስናይ በእቅዱ መነሻ 8 የነበረውን የማህበረሰብ ጣቢያ ወደ 26 ማድረስ ተችሏል። በእርግጥ በእቅድ ዘመኑ 22 ፈቃድ በመስጠት ሽፋኑን ወደ 30 ለድረስ ነበር የታቀደው። ሆኖም 18 የማህበረሰብ ሬዲዮ ፈቃዶችን በመስጠት ቁጥሩን ወደ 26 ከፍ ከማድረግ ባሻገር አፈፃጸሙ በመቶኛ ሲሰላም 77 ነጥብ 3 በመቶ ነው። ነገር ግን ከ26ቱ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡት 16ቱ ናቸው። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ የማህበረሰብ ሬዲዮ እንደ ህዝብ ብሮድካስት በመንግስት ድጋፍ የሚቋቋሙ ባለመሆናቸው የፋይናንስ፣ የቅንጅትና የሰው ኃይል ችግር ስለሚያጋጥማቸው ነው።
ሆኖም የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች የንግድና የህዝብ መገናኛ ብዙሃን የማይሸፍናቸውን አካባቢዎች የሚሸፍን በመሆኑ በአኗኗራቸው፣ በቋንቋቸውና በባህላቸው ተመሳሳይ የሆኑ ሰዎችን ከማገልገል አንፃር የማህበረሰብ ሬዲዮ በእቅድ ዘመኑ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

Page 1 of 2

JoomShaper